የጄኖቫ ቅዱስ መልክ
ከWikipedia
የጄኖቫ ቅዱስ መልክ በጄኖቫ፣ ጣልያን በተገኘው ቅዱስ በርተሎሜዎስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኝ ስዕል ነው። ይህ ስዕል የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ ለመግለጽ እንደታሠበ ይታመናል።
በአንድ ትውፊት ዘንድ፣ ኢየሱስ በሕይወቱ ስብከት ሳለ የኤደሣ (በሶርያ) ንጉሥ 5 አብጋር በበሽታ ታምመው ኢየሱስ መጥቶ እንዲፈውሳቸው አንድን መልእክተኛ ወደ ኢየሩሳሌም ልከው ነበር። ኢየሱስ ወደ ኤደሣ ለመሔድ ግዜ ስላልነበረው፣ ባንድ ጨርቅ ላይ መልኩን በተአምር አሳተመና ከደቀ ማዛሙርቱ ታዴዎስን ጨርቁን ይዞ ወደ ንጉሡ እንዲሔድ ላከው። እንዲህም ሆኖ አብጋር ይህን ጨርቅ ባዩ ግዜ ከበሽታቸው ተፈወሱና ወዲያው ምዕመን ሆኑ። ስዕሉ ደግሞ በተአምር ስለ ተፈጠረ 'ያለ እጅ የተሠራው' ይባላል።
በጥንታዊ ታሪክ መጻሕፍት መሠረት ይህ ታምራዊ መልክ ያለበት ስዕል እስከ 936 ዓ.ም. በኤደሣ ቆይቶ በዚያ አመት ወደ ቢዛንታይን ዋና ከተማ ወደ ቊስጥንጥንያ ተዛወረ። እዚህም ፈረንጆች (መስቀለኞች) ከተማውን እስከ ዘረፉት አመት እስከ 1196 ድረስ እንዳደረ ይባላል። ከዚያ በኋላ ምን እንደሆነበት ባይታወቀም ብዙ ቅጂዎች ስለተደረጉበት በአውሮጳ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አንዳንድ ቅጂ ዕውነተኛው መልኩ እንዳሉ የሚል ልማድ አለ።
እንግዲህ በጄኖቫ ብቻ ሳይሆን በቫቲካን ከተማ ሮማ ተመሳሳይ ስዕል ቢገኝ እሱ እውነተኛው መሆኑ የሚያምኑ አሉ።
በጄኖቫ ያለው ስዕል መገኛ የጄኖቫ ዶጄ (መስፍን) ሌዮናርዶ ሞንታልዶ በ1376 ዓ.ም. ለበርተሎሜዎስ ቤተክርስቲያን እንዳወረሰው ይባላል። በተጨማሪ ሞንታልዶ ያገኘው፣ የቢዛንታይን ንጉሥ 5 ዮሐንስን ቱርኮች በወረሩበት ዘመን እርዳታ ስለ ሰጠ፣ ዮሐንስ ስዕሉን ስለ ወሮታው በምላሽ እንደ ሠጡት ይታመናል።
የጣልያዊት ሊቅ ኮለት ዱፎር ቦዞ በ1961 ዓ.ም. ብዙ ልዩ ትንትና አድርጋ፣ የጄኖቫ ስዕል በሳንቃ ላይ የተለጠፈ ጨርቅ ከወርቃም ከፈፍ በታች መሆኑን ገለጠች።
- ደግሞ ይዩ፦ የቶሪኖ ከፈን
[ለማስተካከል] ዋቢ መጽሕፍት
- Ian Wilson, Holy Faces, Secret Places, Corgi, ISBN 0-552-13590-9