ሐማዚ
ከWikipedia
ሐማዚ ምናልባት በ2400 ክ.በ. ገዳማ የነበረ መንግሥት ሲሆን በምዕራብ ዛግሮስ ተራሮች ከኤላምና ከአሦር መካከል እንደተገኘ ይታሥባል።
ሐማዚ ለሥነ-ቅርስ ጥናት መጀመርያ የታወቀው በዚህ ቦታ ላይ የኪሽ ንጉሥ ኡቱግ ወይም ኡሁብ ድል የሚመዝገብ በጥንታዊ ባለ-ማዕዘን (ኩኔይፎርም) ጽሕፈት የተጻፈ ጽላት ሲገኝ ነበር።
ሌላ ጥንታዊ ጥቅስ ደግሞ ኤንመርካርና የአራታ ንጉስ በተባለ አፈ ታሪክ ተገኝቷል። እዚህ ኡሩክና ኤሪዱ ግንቦች በተሠሩ ጊዜ ስለ ልሣናት መደባለቅ የተለያዩ አገራት ሲዘረዘሩ በመዝሙር ይጠቀሳል።
በሱመር ንገሥታት ዝርዝር መሠረት የሐማዚ ንጉሥ ሀዳኒሽ ኪሽን ካሸነፈ በኋላ በሱመር ላይ ላየኛነት ያዘ። እሱ ግን በተራው በኡሩክ ንጉስ በኤንሻኩሻና ድል ሆነ።
በኤብላ ከተማ በሶርያ በተገኘ የሸክላ ጽላት ላይ አንድ ዲፕሎማቲካዊ መልእክት ከኤብላ ንጉስ ኢርካብ-ዳሙ ወደ ሐማዚ ንጉስ ዚዚ ከብዙ ዕንጨት ጋር ተላከ። እንደ ወንድም ሆኖ ሰላምታ ሰጥቶ በምላሽ ወታድር እንዲልክለት ይጠይቀዋል።
በአዲስ ሱመራዊ ኡር መንግሥት ጊዜ በንጉስ አማር-ሲን ዘመን ሐማዚ ከጠቅላይ ግዛቶቹ አንድ ነበር። በዚህ ዘመን የአገረ ገዥ ስሞች ኡር-ኢሽኩር እና የናምሃኒ ልጅ ሉ-ናና ይታወቃሉ። የኡር መንግሥት ሊወድቅ ሲል (2010 ክ.በ. ገዳማ) ጠቅላይ ግዛቱ የኢሲን አለቃ ኢሽቢ-ኤራ ወረረው።